ገና መክበር ያለበት በመስከረም ወይስ በታህሳስ?
- አዳኙ ካሜራ

- Jan 6, 2019
- 2 min read
Updated: Jan 6, 2019

ገና መክበር ያለበት በመስከረም ወይስ በታህሳስ?
የ ኢየሱስ የልደት ቀን መስከረም 1 በእንቁጣጣሽ እለት ነው! ገናን በታህሳስ ማክበር ስህተት ነው! በተመልዶ ገና እየተባለ የሚጠራው በዓል በ አውሮፓም በ ኢትዮጵያም በ ወርሃ ታህሳስ መጨረሻ ይከበራል። ነገር ግን በመፅሐፍ ቅዱስ እና ከዋክብታዊ ማስረጃዎች መሰረት ይህ ስህተት ነው። ገና ወይም የ ኢየሱስ ልደት መስከረም እንጂ ታህሳስ ሊሆን አይችልም። ታህሳስ በአውሮፓ ይከበር የነበረ የ ፓጋን እምነት የበዓል ቀን ነው። ማስረጃዎችን ላቅርብ 1 መፅሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን በቀጥታ አይናግርም። ነገርን ግን በተዘዋዋሪ መንገድ ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን ከመፅሐፍ ቅዱስ ማወቅ ይቻላል። የኢየሱስን የልደት ቀን ለማወቅ የሚረዳን የሉቃስ ወንጌል ነው። ‹‹በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስሟም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።›› ሉቃ 1፡5-6፡፡ እዚህ ላይ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት ዘካርያስ ከ ''አብያ ክፍል'' የሆነ ካህን መሆኑን ነግሮናል። የ አብያ ክፍል ካህናት ከዳዊት ግዜ ጀምሮ በተሰራላቸው ስርዓት መሰረት በቤተመቅደስ ገብተው የሚያገለግሉት በወርሃ ሰኔ ነው። የአገልግሎት መርሃ ግብራቸው ሰኔ ላይ መሆኑን በተለያዩ የታልሙድ/የኦሪት መፅሐፍት ላይ እናነባለን። ዘካርያስ ከመቅደስ እንደወጣ ሚስቱ እልሳበት ፀነሰች ይላል። ይህ ማለት መጥምቁ ዮሐንስ ሰኔ ላይ ነው የተፀነሰው። የሉቃስ ወንጌል ወረድ ብሎ ድንግል ማርያም በ ስድስተኛው ወር በ ገብርኤል ብስራት ማግኘቱዋን እና መፀነሱዋን ይነግርናል። ዮሐንስ ሰኔ ላይ ከተፀነሰ፣ ኢየሱስ በስድስተኛው ወር ማለትም በ ታህሳስ ወር ነው የተፀነሰው። ታህሳስ ላይ የተፀነሰው ኢየሱስ በዘጠነኛው ወር መስከረም ላይ ተወልዱዋል ማለት ነው። ይህ ግልፅ የሆነ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ነው።
2 ኢየሱስ በተወለደ ግዜ እረኞች ከብቶቻቸውን በሜዳ ላይ ይጠብቁ ነበር ይላል። በዛን ወቅት በ ይሁዳ እና ሰማርያ ታህሳስ ቀዝቃዛ ወር ነው። ከብቶችንም ሜዳ ላይ በታህሳስ ወር ማሰማራት የተለመደ አይደለም። ስለዚህ እየሱስ በፀደይ ወይም በበጋው ወራት መወለዱን መገመት ይቻላል።
3 ለ ሎጀስቲክ አመች ባልሆነ የክረምት ወራት አውግስቶስ ቄሳር የህዝብ ቆጠራ ሊጠራ እንደማይችል መገመት ይቻል።
4 ኢየሱስ በተወልደ ግዜ ታየ የተባለው ኮከብ ነው። በተለምዶ star of the Bethlehem ይባላል። መፅሐፍ ቅዱስ ይህ ኮከብ ሰብአሰገልን ወይም የጥበብ ሰዎችን መራቸው ይላል። አሁን ላይ አብዛኛዎቹ አስትሮነመሮች የተስማሙት በፈረንጆች በ መስከረም 11/12 7 BC በእኛ በ መስከረም 1/2 በ 1 አም significant የሆነ astronomical ከዋክብታዊ ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር ነው። ከዚህ በመነሳት ነው ፈረንጆቹ የሚያከብሩት ልደት እና አዲስ ዓመት ወሩም አመተ ምህርቱም ስህተት መሆኑ የታወቀው።
ስለዚህ በመፅሐፍ ቅዱስ እና ከዋክብታዊ ማስረጃዎች መሰረት ኢየሱስ የተወለደው በመስከረም ወር ነው አመተ ምህረቱም ፈረንጆቹ ከሚያከብሩት 7 ዓመት ወደሁዋላ ያለ ነው። እኛም 7 ዓመት ውደሁዋላ ማለታችን ትክክል ቢሆንም የታህሳስ ወርን መከተላችን ግን ስህተት ነው። ገና እንቁጣጣሽ ነው ። በ እንቁጣጣሽ እለት ነው ኢየሱስ የተወለደው።



Comments