top of page

ቦሌ ቅዱስ ሚካኤል አዲሱ የጦርነት ቀጠና

  • Writer: አዳኙ ካሜራ
    አዳኙ ካሜራ
  • Jan 6, 2019
  • 5 min read

Updated: Jan 6, 2019

ቦሌ ቅዱስ ሚካኤል አዲሱ የጦርነት ቀጠና *★★★*


~ " አለቃው ከቤተክህነት ደብዳቤ ይዞ ስለመጣ የግድ መቀበል አለባችሁ " [ የቦሌ ፖሊስ ።]

~" ጥቁር ጅብ ሸኝተን ነጭ ጅብ አንቀበልም።" [ ቦሌ ሚካኤሎች። ]

~ በእናታችሁ " ለአንድ ሳምንት ብቻ ተቀብላችሁ ሞክሩኝ [ " አለቃ ሩፋኤል [ አቡ ]

~ ይሄ ችግር እንዳይፈጠር ብለን ነበር አቡን የእልቅና ደሞዙን እንደያዘ ወደ ቢሮ ሥራ የመደብነው። [ መምህር ይቅርባይ ]

~ ይሄ ሁሉ እየሆነ እያዩ ብዙዎች ካህናትና ምእመናን ጮጋ ማለትን መርጠዋል። ሁሉም ካልደረሰበት አይንጫጫም። ሰአሊተ ምህረቶች ሲንጫጩ፣ መከራቸውን ሲያዩ የካ ሚካኤሎች ጮጋ ብለው ያዩ ነበረ፣ የካዎች በራሳቸው ሲደርስ እሪሪ ሲሉ ቦሌ ሚካኤሎች ከንፈር ይመጡ ነበር። ዛሬ ራሳቸው ተረኛ ተሸባሪ ሆነው አረፉት። ይሄኔ ሳሪስ አቦዎችና ቅዱስ ዮሴፎች ቦሌ ሚካኤሎችን ሲንጫጩ በራቸውን ዘግተው ዝም ብለው ያዩ ይሆናል።

#ETHIOPIA | ~ አዲስ አበባ ፤ ቦሌ ሚካኤል።

~ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በጣምራ ከደላሎቹ ጋር ፈጠሩት በሚባለው የጋራ ግንባር አማካኝነት በቅርቡ በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ስር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሌለ ቀውጢ የሆነ ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል ውስጥ አዋቂዎች ከወዲሁ እየተናገሩ ነው።

~ ከዘራፊው ጎይቶም ጋር እጅና ጓንት ሆነው ሲሰሩ የነበሩትና አሁን " አላስበላ አለን " ያሉትን የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ይቅርባይን ፓትሪያርኩን ጭምር አስፈራርተው ካስነሱት በኋላ በቀጥታ ያደረጉት ነገር ቢኖር እነ ይቅርባይ በዕጣ እንጂ በድለላ፣ በክፍያ፣ ዝውውርና ሹመት የለም ብለው በቃለ ጉባኤ የወሰኑትን የአለቆች ሹመት የምን ዕጣ ነው በማለት ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ትርምስምሱን አውጥተው ዛሬ በቦሌ ሚካኤል የተፈጠረው ስህተት ተፈጥሯል።

~ ቦሌ ሚካኤሎች ነገ ይገባል የተባለውን አለቃ አንቀበልም በማለት የቤተክርስቲያኒቱን ሁሉንም መግቢያ በሮች ክርችም አርገው ዘግተው የሚመጣውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ቦሌ ሚካኤሎች ቤተ ክርስቲያኑን ለመዝጋት ያነሳሳቸው ዋናው ምክንያት ቀደም ሲል ከሰአሊተ ምህረት በተባረረውና ከዚያም የካ ሚካኤል ሲሾሙት የየካ ህዝብ ጭስ የጠገበ ክትክታ እና መቋሚያ ይዘው አናስገባም በማለታቸው ምክንያት ያለ ሥራ የተቀመጠው የቀድሞው የሰአሊተምህረት አለቃ አቡ ሩፋኤል ወደ ቦሌ ሚካኤል ተመድቦ በመምጣቱ ምክንያት ነው።

~ ይህ እንዳይፈጠር ነበር ዛሬ በግፍ ያባረሩትና ሁሉ እንደየሙያውና እንደዕውቀቱ ይቀጠር በማለት፣ ደግሞም ህዝብ የጠላቸውንና ያባረራቸውን አለቆች በድጋሚ ሌላ ቦታ ለምን ይመደባሉ? ሌሎች አዳዲስ ሰዎች ለምን አስተዳዳሪ አይሆኑም በማለት ሃሳብ በማቅረብ ዛሬ በቦሌ የረብሻው ምክንያት የሆነውን አቡን ለቅዱስ ሲኖዶሱም፣ ለቅዱስ ፓትሪያርኩም ጭምር በማሳሰብ ከእልቅና ሙያ ወደ ቢሮ ሥራ ተመድቦ እንዲሠራ ያስደረገው።

~ ይሄን ያደረገው ግን መምህር ይቅርባይ ይሄን ሲያደርግ ግን ብቻውን አልነበረም። በሊቀ ጳጳሱ አቡነ አረጋዊ ሰብሳቢነትና በአስተዳደር ጉባኤው ሙሉ ድምጽ በቃለ ጉባኤ በማስወሰን ነው። ይቅር ባይ አቡን ጠልቶት አይደለም። አቡን ህዝብ ከጠላው ለምን ከህዝብ ጋር እናገናኘዋለን? ለምንስ ቤተክርስቲያን በአንድ አቡ ምክንያት ትታመሳለች። ዘመኑ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ነው። የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ህዝብ መረጃ በቀላሉ የሚያገኝበት ዘመን ነው። እናም ይሄ ከህዝብ ጋር የተጣላን ሰው ለምን ወደ ህዝቡ በድጋሚ ልከን እንበጠበጣለን በማለት ነበር አቡን የቢሮ ሥራላይ የመደበው።

አቡነ ሳዊሮስ ግን አበዱ፣ አሻፈረኝ አሉ። ምን ሲደረግ? ህዝብ ምን አባቱ ያመጣል። የላክንለትን መቀበል እንጂ ምን አገባው ብለው አሻፈረኝ አሉ። እናም ይሄን ለሌብነት እንቅፋት የሆነን መምህር ይቅርባይን በአድማ፣ በአመጽ ፓትሪያርኩንም በማስፈራራት ከሥራ አስኪያጅነቱ እንዲነሳ አደረጉት።

አቡነ ዲዮስቆሮስም 3 ጊዜ የተባረረውን ኤልያስ ተጫኔን ከበሮ እየመቱ በሽለላና በፉከራ " አሳየናቸው። ልክም አስገባናቸው" በማለት ለአራተኛ ጊዜ በደብዳቤ ወደ ሃገረ ስብከቱ መለሱት።

አሁን የመምህር ይቅርባይ እንባ ሁሉንም ሰላም ይነሳቸው ጀምሯል። አቡነ ሳዊሮስም " ጊዜው የኦሮሞ ነው " በሚል ትምክህት አቡነ ዲዮስቆሮስም ዘመነ ህውሓት በማብቃቱ በትግሬነት የበሉበትን፣ የተሾሙበትን ዘመን ዘንግተው " የራያ ዐማራነት " እንቅስቃሴ ማየሉን ሲያዩ የወሎዬነት ካርዳቸውን ስበው አዲስ ጨዋታቸውን ጀምረዋል። ለዚህ ነው ፓትሪያሪኩን " የምንሎትን ካልሰሙ ከፕትርክናዎ ልናነሳዎት እንችላለን" በማለት አሸማቅቀው " እንደፈቀዳችሁት አድርጉት በማለት ክፍቱን የተዉላቸው።

~ አሁን አዲስ አበባ ለዘረፋ ተመቻችታለች። ቀጨኔ መድኃኔዓለም ሙሉ በሙሉ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የሥጋ ዘመዶችና የሃገራቸው ልጆች ተውጧል። የስልጣን ዘመናቸው በግንቦት ወር ስለሚያልቅ ቶሎ ቶሎ መሥራት አለብን ብለው የሌለ ፋውል እየሠሩም ነው። አቡነ ዲዮስቆሮስም ሆነ አቡነ ሳዊሮስ ከህዝብ ባይጣሉ መልካም ነው። እግዚአብሔርን መፍራቱ እንኳ ቢቀር እንዲያው ሰው ምን ይለኛል ቢሉ መልካም ነው ባይ ነኝ። የሚገርመው ነገር ሁለቱም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለእኔ ለዘመዴ ወዳጆቼ ጭምር ናቸው። የእኔ ዋናው ችግሬ ከእውነት ጋር ተጋብቼ እና ቆርቤ ድርቅ ማለቴ ብቻ ነው። እውነት ደግሞ አግዚአብሔር ነው።

እንግዲህ የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዛሬ የቤተክርስቲያኑን በር ከዘጉት ካህናት፣ የሰንበት ተማሪዎችና ምእመናን፣የተውጣጡ ሰዎችን፣ ደግሞም አዲስ ተልኮ የመጣው አቡንና የጽህፈት ቤት ሠራተኞችን ጭምር ሁለቱንም ሲያነጋግር መዋሉ ነው የተነገረው።

ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ መግባት ባይፈልግም የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ " በኦሮምኛ ቋንቋ መዛት " የፖሊስ ኃላፊዉን ሳያስፈራሩት አልቀረም" ይላሉ የቤተክህነቱ የመረጃ ምንጮቼ። ይሄ ማለት በፊት እነ ተክላይ የሚያደርጉትን አሁን እነ ገመቺስ እየደገሙት ነው ማለት ነው።

በዛሬው ዕለት የቦሌ ክ/ከ ፖሊስ መመሪያ በቦሌ ሚካኤል የተቋቋመውን ኮሚቴ ማናገር እንደሚፈልግ በመግለጹ ወደ ስፍራው ያመሩት ኮሚቴዎች ከረፋዱ 4፡30 እስከ ቀኑ 7፡00 ሰዓት ድረስ በአንድ ጎን አዲሱ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት የማነ ብርሃን፣ የደብሩ ዋና ጸሐፊ መንክር ጥበቡ፣ የደብሩ ም/ ጸሐፊ መንግሥቱ፣ የደብሩ ቁጥጥር ሊቀ ትጉሃን አማረ መረሳ፣ የደብሩ ገንዘብ ቤት አሰፋ ሂሩት፣ የደብሩ ሂሳብ ሹም ፍስሓ፣ ሆነውና ለአዲሱ አስተዳዳሪ ወግነው የቀረቡ ሲኾን በሌላ በኩል ደግሞ የቦሌ ሚካኤል ቤ/ክንን ወክለው የተመረጡ ተወካዮች በተገኙበት ውይይት መደረጉን ነው ከሥፍራው የመጣው መረጃ የሚያመለክተው።

ፖሊስ “ ከሀገረ ስብከቱ ደብዳቤ መጥቶልናል፡፡ በር መታሸጉም አጣሩ ተብለናል፡፡” ቢሉም ከብዙ ጉንጭ አልፋ ክርክር በኋላ ውይይቱ በፖሊስ መምሪያው ኃላፊ ኮሚሽነር ቀጭን ትዕዛዝ “ የተመደቡትን አስተዳዳሪ መቀበል አለባችሁ፡፡ ተቃውሟችሁን ከገቡም በኋላ ወደሚመለከተው አካል ሄዳችሁ ማሳወቅ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን እንዳይገቡ ምንም ዓይነት ክልከላ ማድረግ አትችሉም፡፡” ብለዋል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡት መካከል፡- ሊቀ ትጉሃን አማረ መረሳ፡- “የቢሮው በር መታሸጉን ዓይቻለሁ! ያሸጉት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል!” ያሉ ሲኾን

ጸሐፊውም፡- “መታሸጉን ዓላየሁም ግን ሰምቻለሁ፡፡” በማለት መልሷል።

ፖሊስም “ለምን አልሄዱም?” ላላቸው ጥያቄ “ለህይወቴ በመስጋቴ ነው ” በማለት መልሰዋል።

ከተወካዮቹም በሩ የታሸገበትን ምክንያት ሲያብራሩ፡-

“በሩን የማሸግ እርምጃ የወሰድነው፡- አስተዳዳሪው አለመቀበላችንን ለመግለጽ፣” “መጥተው የከፋ ችግር ከሚፈጠር ይልቅ በዚህ መልኩ ካወቁት እራሳቸው እንዲቀሩና ችግሩን ለመቅረፍ፣”፣ “ሳይታሰብ ቢገቡ ድጋሚ ቤተ - ክህነትም ኾነ ሃገረ ስብከትም መንከራተት ስለማንፈልግ ነው፡፡” በማለት ለፖሊስ ምላሽ ሰጥተዋል።

አዲስ የተመደቡት አስተዳደሪ ሩፋኤል የማነ ብርሃን በበኩላቸው እንዲህ በማለት አስረድተዋል፡-

“ከሀገረ ሰብከት ወደ ቦሌ ሚካኤል መዘዋወሬን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሶኛል። ነገር ግን በማላውቀው ኹኔታ “አንቀበልህም!” ብለውኛል፡፡ ስሜንም በሚያጎድፍ ሁኔታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ባነር ለጥፈዋል፡፡” “ከዚህ በፊት ቀርቦብኝ የነበረው ክስ ተጣርቶ ሐሰት መኾኑ ተረጋግጧል!” “ከፈለጋችሁ ገብቼ እዩኝና ችግር ካለብኝ እንድቀየር አድርጉኝ!”። “ሀገረ ስብከት ማለትም የበላይ አካል ስለላከኝ አንድ ቀንም ኾነ አንድ ሳምንት በሥራዬ ላይ ሆኜ እነሱ ቅሬታቸውን ያቅርቡ። ከዛም ከላይ የሚወሰነውን ውሳኔ ልስማ!” ብለዋል፡፡

ፖሊስ ኮሚሽነሩም “አስተዳዳሪው ከሀገረ ስብከት ተመድበዋል፡፡ ሥራ ይጀምሩ! ‹‹እንቢ!›› የሚል “መብት አለኝ!” የሚል ካለ የራሱን ያድርግ! ነገር ግን በምናረገው ነገር ግን አንድ ኢንች ወደ ኋላ አንልም!” በማለት ምክር አዘል ማስፈራሪያ ለግሰዋል፡፡

በዚህም መሰረት በፖሊስ ኮሚሽነሩ የተነገረውና ያለው ነባራዊ ኹኔታ ከተቋቋመው ኮሚቴ በላይ ስለኾነ የኢ.ኦ.ተ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች፣ የአጥቢያው ምዕመናን በሙሉ “እሑድ ታኅሳስ 28/2011ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ወደ ደብሩ ይገባሉ፡፡” የሚል መረጃ ስላለ ህዝበ ምዕመናኑ የቻለ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዳር በመገኘት፣ ያልቻለ ደግሞ በተጠቀሰው ሰዓት በቤ/ክኑን ግቢ በመገኘት በኃይል እንዳይገቡ ለመከላከልና የቅዱስ ሚካኤልን ቤት እንድንጠብቅም ስንል እናሳስባለን በማለት የቦሌ ሚካኤል ካህናትና ሰንበት ት/ቤት ምዕመናን እንዲሁም የአካባቢው ወጣቶች ጥሪ አስተላልፈዋል።

ለአለቃው የእኔ የዘመዴ ምክር።

አቡ ቤተክርስቲያን የማስተዳደር እንዲህ ያለ ጽኑዕ ፍቅር ካለው ሃብታሞች ሰፈር ባለ ደብር መድቡኝ ብሎ መከራ ከመብባላት፣ ደጋግሞም ከመዋረድ ወደ ጅጅጋና ቀብሪ ደሃር፣ አፋር ሎጊያ ቢመደብ የተሻለ ይሠራል ብዬ እገምታለሁ። እባካችሁ አቡን ቀብሪደሃር መድቡት።

አቡነ ሳዊሮስና አቡነ ዲዮስቆሮስ ግን ነብር አየኝ በሉ። የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ይባል የለ። እንደዚያ ነው። ቤተክርስቲያን ለገንዘብ ብሎ ማመመስ ትርፉ ኪሳራ ነው። በ10 ሚሊየኑም ጉዳይ ገና እናወራለን። ለማንኛውም የሚመጣውን ትርምስ እዚያው ተወጡት። እኔ ግን ከሥር ከስር እየተከታተልኩ መዘገቤን እቀጥላለሁ።

ሻሎም ! ሰላም !

ዘመድኩን በቀለ ነኝ። ታህሳስ 27/2011 ዓም ከራየን ወንዝ ዳር።


Comments


bottom of page