top of page

ሠው ሳይማርና ሳያውቅ በራሱ ላይ አይነግስም!

  • Writer: አዳኙ ካሜራ
    አዳኙ ካሜራ
  • Jan 6, 2019
  • 2 min read

Updated: Jan 6, 2019

ሠው ሳይማርና ሳያውቅ በራሱ ላይ አይነግስም!


ሠው መሆን ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ ጥበቡ የሚገለፀው ሠው ሠውነቱን መኖር ሲጀምር ነው፡፡ ሠው በአካላዊም በመንፈሳዊም ማንነት የሚገለጥ ነው፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊው ማንነቱ እንደፈረስ ጋሪ አካሉን ከፊት ሆነ ይጎትተዋል፡፡ ሠው ያለመንፈሳዊ ሕይወት ምንም ነው፡፡ ነፍስ፣ ሃሳብ፣ ማንነት፣ አስተሳሰብ፣ አመለካከት የሠው መንፈሳዊ መገለጫዎች ናቸው፡፡

ሠው በቁሳዊ ሕይወቱ ነቅቶ በመንፈሱ ከተኛ ሠውነቱ ይጎድላል፡፡ ስጋውን አወፍሮ ሕሊናውን ካመነመነ ሠውነቱ አደጋ ላይ ነው፡፡ በመንፈሱም በስጋውም የነቃ ግን እሱ ብልህ ነው፡፡ ሙሉ ንቃት የሚገኘው ሠው ለነፍሱም ጭምር መኖር ሲችል ነውና፡፡

ለመንቃት መጀመሪያ ማወቅ አለብን፡፡ ዕውቀት ደግሞ የሚገኘው ከውጪው ዓለም ነው፡፡ ከውጪው ዓለም ያገኘነውን ዕውቀት ቁጭ ብለን ከውስጣችን ጋር እናናብበዋለን፡፡ በማናበብ ውስጥ ራሳችንን እንፈልገዋለህ፡፡ ራሳችንን በመፈለግ ሂደት ከውስጣችን ጋር መግባባት እንጀምራለን፡፡ በመግባባት ስሜትን፣ ፍላጎትን፣ ዝንባሌን ወዘተ ነገሮች መግራትና ማስተዳደር የሚያስችል አቅም እናገኛለን፡፡ ከዛም በራሳችን ላይ ድልን እንቀዳጃለን፡፡ የውጪው ዓለምና የውስጣዊው ዓለማችን አንድ ይሆናሉ፡፡ በውስጡ ዓለማችን የውጪውን ዓለም እንመራለን፡፡ የውስጡ የውጪውን ይቀይራልና!

በራሱ ላይ ድል የተቀዳጀ ሠው የውስጡን ጉዞ የጨረሠ ነው፡፡ እዚህ ለመድረስ ግን ተሞክሮ ግድ ይላል፡፡ ራሳቸውን አግኝተው በራሳቸው ላይ ድል ያገኙ ሠዎች ዕውቀትን ለማግኘት ባክነዋል፡፡ ከእነርሱ በፊት በነበሩ የዕውቀት አባቶቻቸው ስር ደቀመዝሙር ሆነው ዕውቀትን ቃርመዋል፡፡ ያለ ዕውቀት ውስጣችንን ብንዋኘው የምናገኘው ምንም ነገር የለም፡፡ መስመጥ ያልሆነ መንሳፈፍ ብቻ! ሠምጦ ውስጡን ያገኘ ግን በልምድ የካበተ ጎበዝ ዋናተኛ ነው፡፡ ከጥልቁ ገብቶ ይዞ የሚመጣው ነገር አለው፡፡

ወዳጆች አዕምሯችን ያልመገብነውን ሃሳብ አይሠጠንም፡፡ ያላጎረስነውን ዕውቀት አያወጣልንም፡፡ ያስቀመጥነውን ነው የምንመነዝረው፡፡ ባንክ የምንገባው ያስቀመጥነውን ለማውጣት አልያም ባስቀመጥነው ላይ ለመጨመር ነው፡፡ ተሞክሮ ማስቀመጥ ግድ ይላል ወዳጆች!

አንድ ሠው ቡድሃን ‹‹ደስታን እፈልጋለሁ ምን ላድርግ?›› ብሎ ጠየቀው::

ቡድሃም ሲመልስ፡- ‹‹በመጀመሪያ “እኔ” የሚለውን የራስ ወዳድ ስሜትህን አስወግድ፡፡ ቀጥለህ ደግሞ ፍላጎትህን ማለትም ምኞትህን አጥፋ፡፡ አሁን አንተ ብቻህን ከደስታህ ጋር ትቀራለህ፡፡››

በማለት መለሠለት፡፡ ነገር ግን እኔነትን ለማጥፋትና ፍላጎትን ለመደምሰስ ተሞክሮ ያሻል፡፡ ልምምድ ይጠይቃል፡፡ ሌሎች የቻሉበትን ማወቅ ለራስ ችሎታ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ሠው ሳይማርና ሳያውቅ በራሱ ላይ አይነግስም፤ በራሱ ዓለም የመነነ ሠው በቂ ዕውቀት ካልጨበጠ ከዓለሙ ጋር አይግባባም፡፡ ‹‹የመነኮሠ በራሱ ነገሠ›› እንዲል ብሂሉ ከምንኩስና በፊት ዕውቀት አልያም ተሞክሮ ወይም ልምምድ ያሻል፡፡ አልያ ልምድ የሌለው በሬ ላይ ሞፈር መጫን ነው የሚሆነው፡፡ መነኩሴውም በራሱ ሳይነግስ ተሳስቶ አሳሳች ይሆናል፡፡

መንፈሳዊ ሕይወት ለሠው ልጅ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሠው ለስጋው ብቻ እየኖረ ሠውነቱን ጥሏል፡፡ የጣለው እውነተኛ ማንነቱን ራሱ ካላነሳው ሌላው ረግጦት ነው የሚልፈው፡፡ ማንነቱን ለማንሳት አዕምሮውን ማንሳት ይጠበቅበታል፡፡ የተኛውን ሕሊና በዕውቀት መቀስቀስ ግድ ይለዋል፡፡ ሕይወት ያለ በጎ አዕምሮ ገሃነብ ናት፡፡

አርስጣጢሊን ለሠው ከሥራ ሁሉ እንደምን ያለ ሥራ ገንዘብ ማድረግ ይገባዋል ቢሉት፡- ‹‹ሠው ገንዘብ ማድረግ የሚገባው ማታውኑ ሠጥማ ጥዋት አብራው ከመስጠም የምትወጣውን መርከብ ገንዘብ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ይህችውም ክፉውን ከበጎው፤ በጎውን ከክፉ ለይቶ የሚያውቅባት ክፋትንና አመፅን ከማድረግ የሚመለስባት (ሲተኛም አብራው የምትተኛ፤ ሲነሳም አብራው የምትነሳ) በተፈጥሮ የተለገሠችው አዕምሮ ናት፡፡›› በማለት መለሠ ይባላል፡፡

ወዳጆች አዕምሯችንን መላልሠን በመስራት የአዕምሯችንን ሠላም እናስጠብቅ የዕለቱ መልዕክት ነው!

ቸር ጊዜ!

__________________________________________





Comments


bottom of page