በጌታ በዓለ ልደት ጭፈራና ዳንኪራ እ እ እ ነውርም፣ ወንጀልም፣ ኃጢአትም ነው። አ ከ ተ መ
- አዳኙ ካሜራ

- Jan 6, 2019
- 3 min read
Updated: Jan 6, 2019
~

*★★★*
★ አዳሜ ስትፈልግ ትፈነዳታለህ እንጂ እውነቱ ይኸው ነው። እያባበሉክ አልነግርህም። ወደህና ፈቅደህ እስካነበብከኝ ድረስ እውነቱን፣ ሃቅ ሃቋን፣ ነጭ ነጯን እግትሃለሁ። ሃላስ፣ ይኸው ነው።
" የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን አሳየን።" መዝ 36፣9።
"ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን፤ እነርሱ ይምሩን፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱን።" መዝ 43፣3"
" በጨለማ እየሄድን፣ በጨለማ ውስጥ ለምንኖር ለእኛ ምስኪን ሕዝቦችህ ብርሃንህን አሳየን፤ በሞት ጥላና በሞት አገርም ለምንኖር ለእኛ ድንቅ የሆነውን ብርሃንህን አውጣልን።" ኢሳ 9፣2።
#ETHIOPIA | ~ ልደተ ክርስቶስ ። " ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። " ሉቃ 2፣ 11።
ዛሬ ዕሁድ ታህሳስ 28/2011 ዓም ነው። የልደተ ክርስቶስ ዋዜማም ነው። የነገውን የጌታን ልደት ለማክበር ሽርጉዱ መቼም አይነገርም፣ አይወራምም። ልደትን በቅዱስ ላሊበላ እንደማክበር የሚናፈቅ መቼም የለም። ቱሪስቱ ሁሉ ነው የሚደመምበት። ወረቡ፣ ዝማሬው፣ ማኅሌቱ መቼም ልዩ ነው።
ዝግጅቱ በየፊናው እንደቀጠለ ነው። ቤተክርስቲያን በሯን ከፍታ ልጆቿን ትጠብቃለች። ዓለምም እንደዚያው በሯን ከፍታ ልጆቿን ትጠብቃለች። ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥተ ሰማያት ዓለም ደግሞ ለገሀነመ እሳት በየፊናቸው እጩ መልምለው ያዘጋጃሉ። ሁለቱም ጋር ይጨሳል። ቤተክርስቲያን ሰማያዊውን የጸሎት ማሳረጊያ ዕጣን በጸሎት አጅባ ልጆቿን ነፍሳቸውን ጭምር በመልካም ጠረን ታውዳለች፣ ልብሱም ልቡም ይቀደሳል። ዓለምም ጋንጃ፣ አጤፋሪስ፣ ሐሺሽና ሺሻ ጥዳ እያጨሰች ልጆቿንም እያስጨሰች ናላቸውን አዙራ፣ አጡዛ በእርኩሰት ትሞላለች።
ምንም እንኳ ብዙዎቻችን ክርስቲያኖች፤ በክርስቶስም ያመኑም ተብለን ብንጠራም፤ አንድ ክንድ መስቀል በደረታችን ወፍራም ማዕተብ በአንገታችን አስረን ብንታይም ነገር ግን እኛ በምንጠራበት በምንታወቅበት ስም እየኖርን የማንገኝ ብዙዎች ነን። ከኃጢአታችን ብዛትና ከሰውነታችን ክፋት የተነሳም በየዕለቱ ልንመላለስበትና በውስጡ ልንኖርበት የሚገባንን የጌታችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የብርሃነ ልደቱን ምስጢር ከእኛ ተሰውሮብን ይታያል። ዘወትር በምንሠራው ሥራ፣ በምናደርገው ድርጊትና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ሁሉ ድንቅና ከአዕምሮ በላይ የሆነው የአምላክ ሰው መሆን፤ የሰውም አምላክ የመሆን ምስጢር በእኛ ዘንድ ምንም ዓይነት ቦታና ስፍራ ያለው አይመስልም ።
ድርጊታችን እና አኗኗራችን ክፉ ሥራችንን ሁሉ ስንመለከተው ክርስቶስ ተወልዶላቸው በመወለዱም ከኃጢአት እስራት ተፈትተው በሚደነቅ ብርሃን እንደሚመላለሱ የሀዲስ ኪዳን ሰዎች ሳይሆን የምንመላለሰው ገና ጌታ መድኃኔዓለም እንዳልተወለደላቸውና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚኖሩት እንደ ዘመነ ብሉይ ዓይነት ሰዎች ኑሮ ነው ስንኖርን የምንታየው። ለዚህ ነው ተቅበዝባዥ፣ ተስፋ ቆየቆረጥን፣ ሌባ፣ ዘረኛ፣ ጎጠኛ፣ መናፍቅ፣ ተጠራጣሪ ወዘተ ሆነን ከኃጢአት ላንፋታ ተጋብተን በስምምነት የምንኖረው ።
እንዲያው ማን ይሙት ሳይዋሹ ለራስዎ ይንገሩና ይህን መልእክቴን የማንበብ አጋጣሚውን ያገኙ እርስዎ መጪውን የጌታን ልደት በምን ዓይነት ሁናቴ ነው ሊያከብሩ የተዘጋጁት ? የትስ ነው ቀጠሮ የያዙት?
"ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ " እያሉ በጌታ መወለድ እግዚአብሔር ሲያመሰግኑ፤ መንጋቸውንም በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ እንዳደሩት እረኞች እና ከመልአኩም ጋር እንደነበሩት ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርንም በማመስገን ነው ወይንስ በሌላ?????
ደግሜም እላለሁ እርስዎ መጪውን የጌታን ልደት የት ለማክበር አቅደው ተዘጋጅተዋል?
" በሌሊት ጧፍና ሻማ እያበሩ፣ በካህናትና በመዘምራን ቅዳሴና ዝማሬ፣ በሽብሸባና በእልልታ በብርሃን ተጥለቅልቀው፣ ነጭለብሰው ነጭም ተጎናጽፈው በአቅራቢያዎ ካለ ቤተክርስቲያን ወይንስ ???
እሳት በሆነ በማይቀመስ የአንድ ሙክት መግዣም በሆነ ብር ቁራች ትኬት ገዝተው፣ ቆርጠው ወይም ተቆርጦልዎት በዲጄና በባንድ ታጅበው በዳንስና በእስክስታ በጨለማው ዲም ላይት መብራት ጠቁረው፣ገበናን የሚያጋልጥ ልብስም ለብሰው፣ ጨለማን ተጎናጽፈው ያለልክም በመብላትና በመጠጣት በስካርም ደግሞም በድብድብ አካልዎንም ከፍ ሲልም ህይወትዎንም አጥተው በክለብ፣ በቡና ቤት ወይስ በሆቴሎች ለማሳለፍ ነው የወሰኑት?
የጌታን ልደት በዳንኪራና በጭፈራ፣ በዳንስና በእስክስታ፣ በመጠጥና በስካር በዝሙትም ማክበር በፍጹም ክርስቲያናዊ አስተምህሮ አይደለም። ዓለም ላንቃዋ እስኪሰነጠቅ ድረስ በጋዜጣ፣ በበራሪ ወረቀቶች፣ በኢንተርኔት፣ በፌስቡክ፣ በራዲዮና በቴሌቭዥን ጭምር የኑልኝ ጥሪዋን በየሰከንዶች ልዩነት ሳትሰለች ማስታወቂያ እያስነገረች እየተጣራችም ትገኛለች።
ስንቶቻችን ነን ትኬት ገዝተን ወደ አስደናቂው ጨለማ ለመጓዝ የቀኑን መድረስ፣ የዋዜማውን ምሽት እየጠበቅን የምንገኝ ??? ዘፋኞች ድምጻቸውን እየሳሉ ነው፣ ጨፋሪዎችም እንዲሁ በዝግጅት ላይ ናቸው። ሴተኛ አዳሪዎችም " መኳኳያ ጌጦቻቸውን፣ ወንዶችን ጠልፎ መጣያ አሸንክታባቸውንም" በሚገባ አዘጋጅተው ቀኑን ታጥበውና ታጥነው ዕለቱን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የቡና ቤት መብራቶች ወደ ደም መሳይ ቀይ ቀለምነትና ድቅድቅ ጨለማነት ተቀይረው ተዘጋጅተዋል። ቀዩ የሲኦል እሳት፤ ጨለማውም የጥልቁ ምሳሌ ሆኖ ተዘጋጅቶ እየጠበቀ ነው። በእንዲህ ዓይነት ፍጹም ያለቀለት ኃጢአት ያከበርነውን "በአል" እንዴት ለጌታ ሰጥተን እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን ልንባባል እንደፍራለን? በፍፁም ወንጀል ነው። ነውር ነው። ኃጢአት በደልም ነው። መልሱን ደግሞ ሁላችንም እናውቀዋለን። ሁላችንም ።
በክርስቶስ መወለድ የሚያምን ሰው እንዲህ የሥጋ ሥራ አይሰለጥንበትም። የመንፈስ ፍሬ ጎተራ ይሆናል እንጂ። የሥጋን ሥራ ጌታ መድኃኔዓለም ክርስቶስ " ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ፤" ናቸው እያለ በወንጌለ ማርቆስ 7፣22 ላይ ሲነግረን ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ በምእራፍ 5 ፣ ከቁጥር 19–21 ድረስ " የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው" እርሱም ፥ዝሙት፥ ርኵሰት ፣ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው በማለት በዝርዝር አስቀምጦአቸው ሲያበቃ፤ አስቀድሜም ይላል" አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም" በማለት እርግጡን ይነግረናል።
እናም ተወዳጆች ሆይ ! እስከ ጌታ ልደት ድረስ ሁላችንም እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ጌታ ሆይ " ተገለጥልን፣ አብራልን፣ ባርከን፣ ቀድሰን፣ ደስሰንም፣ ከገባንበት የኃጢአት ማጥና ጭቃ ውስጥ ክንዳችንን ይዘህ አውጣን፣ " የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን አሳየን።" መዝ 36፣9 ፣" ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን፤ እነርሱ ይምሩን፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱን።" መዝ 43፣3" በጨለማ እየሄድን፣ በጨለማ ውስጥ ለምንኖር ለእኛ ምስኪን ሕዝቦችህ ብርሃንህን አሳየን፤ በሞት ጥላና በሞት አገርም ለምንኖር ለእኛ ድንቅ የሆነውን ብርሃንህን አውጣልን።" ኢሳ 9፣2 እያልን አብዝተን ልንጸልይ ይገባል።
ደግሜ እላለሁ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን፤ አደረሳችሁ።
ሻሎም ! ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ ። ታህሳስ 28/2011 ዓም ከራየን ወንዝ ዳር ።
📷



Comments