"ማሰብና በአግባቡ መኖር የእናንተ ፋንታ ነው !"
- አዳኙ ካሜራ

- Jan 6, 2019
- 2 min read
Updated: Jan 6, 2019

ይህችን ማለፊያ ወግ አብረን እናጣጥማት ዘንድ ወደድኩ ። ሰውዬው በዓመቱ ወደ ቁልቢ እየሄደ የመልዓኩ ገብርዔልን ታቦት ያነግሳል ። "እስከ መቼ በድህነት እንኖራለን ? ...ምናለ አንድ ቀን የገንዘብ ዝናብ ብታወርድልን ...ላንተ ምን ይሳንሃል ?" እያለ ይለማመናል ። "ፀሎቴን ከሰማኸኝ አንድ ባኮ ሻማ አስገባልሃለሁ" በማለት ከአንድም ሁለቴ ተስሏል ። "ተዓምር አያልቅም" እንደሚሉት ሆኖ ስለቱ ሰመረለት ። አንድ ሌሊት የሰማይ በር ተበረገደ ። የገንዘብ ዝናብ ጣለ ። ሰውዬው የሚኖርባት ከተማ በገንዘብ ባህር ተጥለቀለቀች ። ሁሉም ሰው ሀብታም ሆነ ። ሲፈልጉ ፤ ሲመኙና ሲያምራቸው የነበረውን ሁሉ እየተጋፉ መሸመት ጀመሩ ። ዳቦ የፈለገ ለባለ ዳቦው መቶ ብር እየወረወረ "ቶሎ ስጠኝ ፤ መልስ አልፈልግም" ሲል ፤ ሌላ ዳቦ ፈላጊ ሁለት መቶ ብር ሰጥቶ ዳቦውን ለመውሰድ ይሽቀዳደማል ። ሁሉም ዕቃ ላይ እንደዛ ሆነ ። ነጋዴዎች ሸቀጦቻቸውን አሟጠው ፤ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የሚፈልጉትን ለመግዛት ወደ ሌላ ቦታ ሲሮጡ ፤ ሌላ ቦታ የሚነግዱትም እነደነሱ ዕቃቸውን ጨርሰው ፣ ሱቃቸውን ዘግተው ፣ለራሳቸውየሚፈልጉትን ለመግዛት ወደነሱ ሲመጡ ይተላለፋሉ ። ሁሉም ነገር በጥቂት ሰዓት ተጠናቀቀ ። ከተማው በእጁ የገባውን እንዳይነጠቅ ፤ በሩን ዘግቶ ተቀመጠ ። አንዱ የሌላውን በር እያንኳኳ "አንድ ዳቦ ወይም ግማሽ ኪሎ ስኳር ካለህ በሚሊዮን ብር ሽጥልኝ" ሲለው ፤ "አንተ ካለህ በአስር ሚሊዮን ብር እገዛሀለሁ" ማለት ተጀመረ ። ከተማዋ ትንፋሿንዋጠች ። ሰውዬው አዘነ ። እግዜርን ለማግኘትም ተቻኮለ ። ........................... እግዜርንም አገኘው ። በእጁ የያዘውን የስለት ሻማ ለጠባቂው መልዓክ አቀብሎ ፣ ወደ እግዜር ዞር አለና ... "ምን አደረግንህ ? ምን በደልንህ ?" ሲል ጠየቀ ። "ምንም" በማለት መለሰለት ፤ እግዜር ። "ታዲያ ለምን ጨከንክብን ? " "አልጨከንኩም ።" አለውና ወደ ሻማው እያመለከተ "አሁን አንተ ሻማ አመጣህልን ፣ በምንፈልግበት ጊዜና ቦታ እያበራን እንጠቀምበታለን ፣ ብርሃን የምንፈጥረው እኛ ነን ፣ አንተ የሰጠኸን ሻማውን ነው ።" "እና ?" "እኔም ጭንቅላት ሰጥቻችኅለሁ ፣ ገንዘብ አዝንቤላችኅለሁ ፣ ማሰብና በአግባቡ መኖር የእናንተ ፋንታ ነው ።" አለው ። ............................. እንዲህ ነው እንግዲህ ወዳጄ ! ፤ የተሰጠንን መክሊት ፤ የወረደልንን መና እንዴትና በምን አግባብ መጠቀም እንዳለብን ማወቅ የእኛ ነው ። በሩን ያንኳኳ ይከፈትለታል እንጂ የቤቱ ባለቤት ጎትቶ ወደ እልፍኙ አይወስደውም ። "ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም " የሚለው ብሂልም ይህንኑ እውነታ ያረጋግጥልናል ። ............................. ተመስገን



Comments