ከርታታው ይሁዲ !
- አዳኙ ካሜራ

- Jan 6, 2019
- 2 min read
Updated: Jan 6, 2019
......................... በኢየሱስ ክርሰቶስ ልደት ዋዜማ ላይ ቆሜ ከስቅለቱ ጋር የተያያዘ ወግ እነሆ ስላችሁ አንድም ሞቱ ከቤተልሄም ውልደቱ ጋር የሚተረክ በመሆኑ ሁለትም ደግሞ የስብሃት ለአብ ዝክር ስለሆነብኝ ነው ። እንግዲህ ወደ ወጋችን እንሂድ ። ........................... የዛሬ ወጋችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕለተ ስቅለት ፤ አርብ ተሲያት ላይ መቼቱን አድርጓል ። አርብ ተስያት ጌታ ኢየሱስን መስቀል አሸክመው እየገረፉ ፣ እየተሳለቁና እየተዘባበቱበት ስቅለቱ ወደ ሚፈፀምበት ስፍራ እየጎተቱና እየገፈተሩ እ የወሰዱት ሳለ ፤ ኢየሱስ በማለፊያ መንገዱ በምትገኝ አንዲት ሱቅ ስር ጥላ አጥልቶ ተመለከተ ። ለአንድ አፍታም ከፀሀይና ወበቅ ለመጠለል የቅፅበት እረፍት ናፍቆ እንደመቆም ሲሞክር ፤ ድርጊቱን ቆሞ ሲመለከት የነበረው ባለ ሱቅ "ወንጀለኛ አናስተናግድም ፤ መንገድህን ቀጥል !" ሲል ወደ ፀሀዩ መልሶ ገፈተረው ። ኢየሱስም የቀረውን ትንፋሽ አሰባስቦ "እኔስ እየሄድኩ ነው ፤ አንተ ግን እስከምመለስ እዚህ ሆነህ ትጠብቀኛለህ ።" ሲል መለሶለት መስቀሉ እንደተሸከመ ጉዞውን ቀጠለ ። በወቅቱ ይሁዲው ባለ ሱቅ በግምት የሰላሳ አመት ጎልማሳ ነበር ፡፡ ..................................... ጊዜ አለፈ ፡፡ ጌታ ሲሰቀል ህፃናት የነበሩት አደጉ ፣ ጎረመሱ ፣ ሸመገሉ ፡፡ እና 'እዚሁ ትጠብቀኛለህ' የተባለውንና መንከራተት የተፈረደበትን ሰውዬ "እኛ ተወልደን አረጀን ፡፡ አንተ ግን እንኳን አርጅተህ ልትሞት ፤ እስከ ዛሬ አንዳች ለውጥ አላየንብህም ፡፡ ምን ማለት ነው ?.. " በማለት ሁልጊዜ በጥያቄ ቢወጥሩት ወደ ሌላ ከተማ ለመሰደድ ተገደደ ፡፡ በእዚያም ንግዱን ቀጠለ ፤ ወዳጆችንም አፈራ ፡፡ እነርሱም እያረጁ ሲያለፉ ፤ ልጆቻቸው ተተክተው አድገው ፣ ማርጀት ሲጀምሩ "እኛ እያየኸን ተወልደን አረጀን ፡፡ አንተ ግን ዛሬም ያው ነህ "ሲሉት ፤ ወደ ሌላ ከተማ ሲሰደድ . . . የትም ቢሄድ የትም ፣ ያው የመኖር ቀምበር እየሰለቸው ሞትን እየተመኘ ሄደ ፡፡ የሞቱንም መንገድ ለማግኘት ዕለት በዕለት አደንና ኀሰሳ ጀመረ ፡፡ ጥቁር ሞት [The Black Death ] የተባለው በሽታ የአውሮፓን ህዝብ ሶስት አራተኛውን እንደፈጀ ሲነገር ከርታታው ይሁዲም ሞትን ፍለጋ ወደ እዚያ ሄደ ። በእዚያም ተላላፊውንና ገዳዩን በሽታ በመፍራት ወላጆቻቸው ወይም ልጆቻቸው በባዶ ቤት ጥለዋቸው የሸሹትን ታማሚዎች አቅፎና ደግፎ ቢያስታምማቸውም ከሞት ግን ሊተርፉ አልቻሉም ። ሞት ብዙዎችን እንደ ቅጠል እያረገፈ ቢገኝም ከርታታው ይሁዲን ግን ተፀይፎት ያልፋል ፡፡ ጦርነት ወደ ተነሳበት አገር እንደ ቅዱስ ገብርኤል ፈጥኖ ይደርስና ደካማ በመሰለው ወገን አንፃር ተሰልፎ ግምባር ቀደም ሆኖ ይዋጋል፣ ይጨፈጭፋል ፤ ሆን ብሎ ለጦር ፣ በሚቀጥለው ዘመንም ለጥይት ደረቱን ይሰጣል ፡፡ ሞት ተፀይፎት ሳይጨርፈው ያልፋል ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ይሁዲያችን የማያውቀው ሀይል አስገድዶ በየሀምሳ አመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይወስደዋል ። "ዛሬ ጌታ ኢየሱስ ወደዚያች ነጃሳ ሱቄ ተመልሶ ብንገናኝስ ? " እያለ ይመኛል ፤ ይፀልያል፡፡ እስከ ምፅዓት ድረስ ፤ ሰዓሊ ለነ ቅድስት ። .......................... ማስታወሻ [ዘነበ ወላ]



Comments