top of page

"ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም" አለ ሌኒን። *★★★*

  • Writer: አዳኙ ካሜራ
    አዳኙ ካሜራ
  • Jan 6, 2019
  • 4 min read

Updated: Jan 6, 2019

~ ወዳጄ ምንም ማድረግ አይቻልም። "ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም" አለ ሌኒን። *★★★*

★ ከዚህ በኋላ ነው እነ አጅሬ መከባበር፣ እነ አቶ መደራደር የተባሉት ጎምቱ ቃላት በተራቸው ሰተት ብለው ተግተልትለው ሲመጡ ማየት።

… ኢትዮጵያችን ለዐማራው ምሬት ለሌላው መሬት የምትሸነሽን ካርታም እየሳለች የምታድል መሆን የለባትም።

… ኢትዮጵያችን ለዐማራው #አጋሰስ ለሌላው #አምቡላንስ የምታድል መሆን የለባትም። አከተመ ። ይኸው ነው።

#ETHIOPIA | ~ አዲስ አበባ ~ ሸገር ~ አዱገነት =

★ በመከራ በሚገኝ የሰው ሚድያ በአጭር ደቂቃ ውስጥ እንዲህ የ100 ሚልዮን ህዝብን አንጀት የሚያርሱ ትንታጎች ካየን ዐማራው የራሱ ሚዲያ ኖሮት 24 ሰዓት ቢውልና ቢያድርብን ምን እናይ የሆን። ዐማራ ሆይ የቀረህ ሚዲያው ነው። እሱ ላይ ሙትበት። የቀረው ይቅር ነግሬሃለሁ። እደግመዋለሁ ሚድያው ላይ ሙትበት። አከተመ።

የዛሬውን የዋልታ ቴሌቭዥንን የኤልክላሲኮ ደርቢ የመሰለ ፍልሚያ ዓይኔን ሳልጨፍን፣ ቅድቤንም ከፍና ዝቅ ሳላደርግ፣ ለሽፋሽፍቶቼም እረፍትን ሳልሰጥ እንዲሁ ፍጥጥ እንዳልኩ ትንፋሼን ውጬ ደግሜ ደጋግሜ ዓየሁት። ዓየሁት አይገልጸውም ከምር ደጋግሜ ቀጸልኩት።

ጋዜጠኛውም ትክክል ነበር። እሱ ነው ኮርኩሮ፣ ኮርኩሮ ትንታጎቹን ወጣቶች መድኃኒት የሆኑ ፈዋሽ ቃላቶችን እንዲተፉ ያደረጋቸው። ጋዜጠኛው የፈለገ ተልእኮ ይኑረው አይኑረው የራሱ ጉዳይ ነው። አይመለከተንምም። ከሰማይ በታች ያሉ ጥያቄዎችን የመጠየቅ ሙሉ ሥልጣንና መብትም አለው። ጋዜጠኛው ልጆቹን አሸማቅቄ አፋቸውን አስይዛቸዋለሁ ብሎም ተወራርዶ ይምጣ ወይም በሌላ ብቻ በፈለገው መልኩ ይምጣ እንኳንም ጠየቃቸው። እንኳን አዋራቸው። እንኳንም ኮረኮራቸው። ስለጠየቃቸው ስለሞገታቸውም ነው ብዙዎች የተፈወሱት።

በዛሬው ቃለ መጠይቅ ጋዜጠኛው ራሱ እጁን በአፉ ጭኖ ልቡን ከፍቶ ፍዝዝ፣ ድንዝዝ ብሎ ከመስማትና ከመመልከት ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረውም። ምንም ስላችሁ ከምሬ እኮ ነው። ምንም።

በእኔ በኩል የዘመናት ህልሜን ፍንጭ በሁለቱ የአብን ትንታግ ወጣቶች ውስጥ ወገግ ብሎ ሲንቦጎቦግ ዐይቼዋለሁ። ተመልክቼዋለሁም። እጅጉንም ደስ ብሎኛል። ሻማዬንም አበራሁ። እልልል ማለት ግን አልቻልኩም። ያለሁበት ቦታና ሰዓት ይህን እንዳደርግ ስለማይፈቅድልኝ። ምክንያቱም ስደተኛ ነኛ።

የዐማራው ነገድ እስከዛሬ ያጣው ይሄን የመሰለ ዕድል ነበር። እየተገደለ የማያለቅስለት፣ እየተሰደደ የማይሟገትለት፣ ዘሩ እንዲጠፋ፣ እንዲገረፍ፣ እንዲጠፋ ሲደረግ እያየ ለወግ ያህል እንኳን ከንፈሩን የማይመጥለት ወኪል አጥቶ በቅኝ ግዛት ወስጥ መክረሙ ነበር ይቆጨኝ፣ ያንገበግበኝ የነበረው። ዐማራ ሆይ ! በመጨረሻም እንኳን ደስስ አለህ። እግዚአብሔር ራሱ በፈቀደው ሰዓት የራስህን ልጆች አስነስቶ የመበደልህን፣ የመገፋትህን ዘመን ሊያስወግድ እነዚህን የመሰሉ ትንታግ ልጆች ስለሰጠህ ፈጣሪህን አመስግን። ዐማራ እኮ እንደ ኤርትራዊው በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰ፣ እና ትግራዋዩ ከበደ ጫኔን በመሰሉ ጥቂት እንኳ ለዐማራው በማይራሩ ጨካኞች እየተመራ በቁሙ ዐይኑ እያየ ጆሮውም እየሰማ እንዲቀበር ተፈርዶበት የነበረው።

ዐማራ ዐማራም ነኝ፣ ኢትዮያጵያዊም ነኝም ሲል ያለ ርህራሄ የሚወቀጥ፣ እንዲሸማቀቅም ፖሊሲ ተቀርጾለት መከራውን የሚያይ ምስኪን ህዝብ ነበር። ምን አልባትም አሁን ትውልዱ የተዋለበት፣ የተደረተበት የሱዳን አዚም ከሽፎ ባይባንንና ባይነቃ ኖሮ ዐማራው በመጨረሻም የኩርዶች ዕጣ ይደርሰው፣ ሀገር አልባም ሆኖ ነበር የሚቀረው። አሁን ከዚያ ማጥ እንደምንም ታግሎ እየወጣ ያለ ይመስላል። ዐማራ ነኝ ሲል ሽምቅቅ የማይለው ትውልድ መፈጠሩ በራሱ ለዚህ አባባሌ ዓይነተኛ ምስክር ነው።

ዛሬ ደግሞ በዋልታ ቴቪ ስንኮመኩም ያመሸነው ነገር ከምር ገራሚ ነበር። አጅሪት ህወሓት ላለፉት 45 ዓመታት እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቆጥሮ ዐማራውን በሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ዘንድ ይዋረድበት ዘንድ በካድሬዎቿ አፍ ውስጥ እንደማስቲካ ሳይሟሟ እንዲቀመጥና በየመድረኩ ይመነዠክ ሲላመጥም ይኖር የነበረውን የስድብና የማሸማቀቂያ፣ የካድሬውም ሁሉ አፍ መፍቻ ተደርገው የተቀረፁና ሁሉም እየተነሳ ቂጣ በቀደደው አፉ በየመድረኩ አፉን ሲከፍትበት የነበረውን፣ እስከዛሬም ድረስ ዐማራው እንደስድብም ይቆጠርበት የነበረውን እንደ #ትምክህተኛ ዓይነቱን ቃል ያለሰቀቀን ሁላቸው ዐማሮች የሚመኩበት ሆነው እርፍ እንዲል፣ የዐዋጅ ያህልም እንዲለፈፍና በሁሉ ሰው ጆሮ እንዲደመጡ የሚያደርጉ ወጣት የዐማራ ፈርጦች ስናይመበት አመሸን።

አቤት ድፍረት፣ አቤት እውቀት፣ አቤት ኮንፊደንስ፣ ገራሚ ነበር። እንደ ጊዮን እንደወንዙ ፍስስ፣ እንደ ጀማ፣ እንደ በሽሎ፣ እንደ ዛሪማ ወንዝ ጥርት ያሉ ቃላትን የሚያወርዱ፣ እንደ ነጩ የጎጃማ ማኛ ጤፍ እንጀራ የሚበሉ፣ እንደ ወሸራ ቅኔ የሚመስጡ፣ ለጆሮ የማይጎረብጡ፣ ሌላውን ኢትዮጵያዊ የማያስቆጡ፣ በድፍረትም የሚተነትኑ፣ ሌላውም እንዲማር፣ እንዲያውቅ እንዲረዳቸው የማድረግ ኃይላቸው ከጣሪያ በላይ የሆነ እሳት የላሱ፣ እሳት የሚተፉ ከሰባኪም በላይ ፍዝዝ አድርገው አንጀት የሚያርሱ ከጎልማሳም ዝቅ፣ ከህጻናትም ከፍከፍ በጣም ከፍ፣ ወጣት የነብር ጣት የሆኑ አንደበተርቱዕ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ዐማሮች ተከስተው አንጀቴን አራሱት። ቅቤ የለም እንጂ አሁን ነበር ቅቤ አጠጡኝ ማለት።

በዛሬው ቃለመጠይቅ ከሰይጣን በቀር ፍጥረታት በሙሉ ይከፋሉ ብዬ አላስብም። ብዙዎች ዐብን ስለተባለ የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን ዐብን ስለተነሳበት ዓላማና ስለሚጮኽለት ህዝብ ከዚህ በፊት በተንሸዋረረ መልኩም ቢሆን የነበራቸውን አረዳድ በደንብ የሚያጠራላቸው እንደ ጠበል ባለ ፈዋሽ ቃላት እንዲፈወሱ እንዳደረጉ አምናለሁ። ብዙዎችንም ዐማራ ሆነው እዚያም እዚህም ከመርገጥ እንደታደጓቸውም አምናለሁ።

ዐማራነት ከኢትዮጵያዊነት አይጋጭም። ዐማራን ስትፍቀው ባንዳ ሆኖ አታገኘውም፣ ጣሊያንና የጣሊያን ፈሽስት ዲቃለ ሆኖም አታገኘውም። የግብጽና የዐረብ ተላላኪም ሆኖ አታገኘውም። ዐማራ ዐማራ ነው። የራሱ መገለጫ፣ ባህል፣ ማንነት፣ ስብዕና ያለው ኩሩና ሃይማኖተኛ ህዝብ። ዐማራ ቢያኮርፍ እንኳ ከኢትዮጵያ ውጪ ይሸሽ ይጠጋበት፣ ይደበቅበት ሀገር እንኳ የሌለው፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት 3 ሺ ሚስማር ተጠቅጥቆ የተሰፋ፣ ንቅንቅ ማለት የማይችል ነገድ ነው። እናም የዐማራ ብሔርተኝነት ለማንም ስጋት አይደለም። አይሆንምም። እስከዛሬም ሆኖም አያውቅ።

በእኔ በኩልበይሄን ቀን ነበር ስጠብቅ የነበረው። ይሄ ቀን እንዲመጣ ነበር ስጮህ የነበረው። ይሄ ቀን እንዲመጣ ነበር ስሳል፣ ስሰደብ የነበረው። ዛሬ በልደተ ክርስቶስ ዋዜማ ስዕለቴ ሰምሯል። ከምር መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ብሩህ ነው። ኢትዮጵያን ከፈጠሩ ህዝቦች መካከል ዋነኛው ዐማራ ራሱንም ሌሎችንም ወድዶ፤ በጋራ ሀገራችን ውስጥ የሚገባኝን ድርሻ ስጡኝ ብሎ በዚህ መጠን በድፍረት ቅሽሽ ሳይለው ሲሞግት በማየቴ ከምር አርክቶኛል።

ጋዜጠኛውም ተወያዮቹም ተባረኩልኝ። አዎ ነፍጠኛ ነን። አዎ ትምክህተኛ ነን ብለው በአንድ ዓመት የማይዘለቀውን ትንተና ነው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፈትፍተው ያጎረሱን። በዚህ ቃለመጠይቅ ውስጥ የተሰደበ ሰው የለም። የተዋረደ ነገድ የለም። የተጎነተለ ብሔር ብሔረሰብ የለም። መብት ነው የተጠየቀበት። እነሰው ልቆጠር የሚል ድምጽ ነው የተሰበከበት። ለሌላው ስጋት ፀብ አጫሪ ቃል የሌለበት እውነት የተሰበከበት ግሩም የሆነ መርሐ ግብር ነበር። ክርስቲያንም፣ በለጠና ጋዜጠኛውም ሁላችሁም አርክታችሁኛል።

እናም ዐማራ ሆይ ! የማንንም መብት ሳትነካ፣ ለለውጡም እንቅፋት ሳትሆን አንተም እንደሌሎች ነገድህን ለመታደግ ተሰባሰብ፣ ተጠራራ፣ ተነጋገር፣ ተደራጅ፣ ድምጽህንም አሰማ። የሌሎቹ በነገዳቸው መደራጀት ኢትዮጵያን አይጎዳም ከተባለ የዐማራው በነገዱ መደራጀት ኢትዮጵያን የሚጎዳበት ምንም ምክንያት የለም። እናም አዳሜ ድምጽ ቀንሱ። ብትችሉ እርዷቸው ያለበለዚያ ጮጋ በሉ። ዐብይና ለማን እየደገፋችሁ ዐብን ላይ መንጫጫቱ ፌር አይደለም። ኡስስስ አትረብሿቸው።

ከዐማራ ጤፉን ለምግብነት፣ ጎበዛዝቱን ለወትድርና፣ ወንዞቹን ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ገንዘቡን በግብር ስም ለሀገሪቱ ሌቦች ካዝና መሙያነት ብቻ መፈለግ አግባብነት የለውም። ነውርም፣ ኃጢአትም ወንጀልም ነው።

★ ጥቂት ምክር ለዐማሮች እባካችሁ ያልነቃችሁ ንቁ። ከራሳችሁ በላይ ስለራሳችሁ የሚያውቅ ስለሌለ ለሌሎች ተተናኳሾች መልስ በመስጠት ጊዜያችሁን ቀርጥፋችሁ አትብሉ። ሌሎች ስለእናንተ እንዲጮሁላችሁ አትጠብቁ፣ አጀንዳ ስጪ እንጂ አጀንዳ ተቀባይ አትሁኑ። ራሳችሁ ለራሳችሁ ጩሁ። የሰው ሚዲያ ደጅ አትጥኑ ። የራሳችሁን ዓለም አቀፍ ሚዲያ አቋቁሙ። አንድ ዐማራ ለሁሉም ዐማራ ፤ ሁሉም ዐማራ ለአንዱ ዐማራ የሚለውን መፈክር ተግባራዊ አድርጉ። በቃ ዳይ .! ወደ ሥራ .! የምን ጫጫታ ነው?

ከእንግዲህ ወዲህ ግን "ዐማራውን ገድላ የምትኖር ኢትዮጵያ የለችም። ወደፊትም አትኖርም። ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ እኩል የምታጎርስ ደግ እናት መሆን አለባት እንጂ ለዐማራው ሬት፣ ለሌላው ማር የምታጎርስ መሆን የለባትም። ለዐማራው ድኽነት ለሌላው ሀብት የምታወርስ መሆን የለባትም። ለዐማራው ሞት ለሌላው ህይወት የምታከፋፍል መሆን የለባትም። ለዐማራው መሃይምነት ለሌላው እውቀት የምታበራ ማሾ መሆን የለባትም። ለዐማራው ምሬት ለሌላው መሬት የምትሸነሽን ካርታም እየሳለች የምታድል መሆን የለባትም። ለዐማራው አጋሰስ ለሌላው አምቡላንስ የምታድል መሆን የለባትም። አከተመ። ይኸው ነው።

ሻሎም ! ሰላም !

ዘመድኩን በቀለ ነኝ። ታህሳስ 28/2011 ዓም ከራየን ወንዝ ዳር።






Comments


bottom of page