top of page

ዘረኝነትን አውድመን አዕምሯችንን እንደገና እናስጀምር!

  • Writer: አዳኙ ካሜራ
    አዳኙ ካሜራ
  • Jan 6, 2019
  • 2 min read

Updated: Jan 6, 2019



ዘረኝነትን አውድመን አዕምሯችንን እንደገና እናስጀምር! (Format racism and Restart our mind) (እ.ብ.ይ.)

ወዳጄ ሆይ… ሐገራችን ታማለች፡፡ ሕመሟም እኛው ነን! መድሐኒቷም እኛ! ያሳመምናትም እኛ! የምናክማትም እኛ! ራስምታቷም እኛ! ቁርጠቷም እኛ! ፈዋሽዋም እኛ! ሐገርህ ሐገሬ ሃብት ሳያንሳት፣ ታሪክ ሳይጎድላት፣ ጥበብ ሳታጣ በድህነት መንከራተቷ፣ በእርስበርስ ጦርነት መታመሷ የእኛው ችግር ነው፡፡ ወገኑን የሚጠላና የሚገፈትር ትውልድ የዘመኑ ክሽፈት ነው፡፡ ሐገሩን ንቆ የፈረንጅ ሐገር ቁስ የሚናፍቅ ትውልድ በበዛበት ሐገር ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ለሐገሩ የሚኖርና አዲስ ሃሳብ የሚፈጥር፤ ግለሰባዊና የሃሳብ ልዩነትን የሚያከብር፣ ወገኑን የሚያቅፍ ትውልድ ማፍራት ግድ ይላል፡፡

‹‹የሐገሪቷ ሁኔታ የሕዝቧ ሁኔታ ነው›› እንዲል የኢቶዮጵ ደራሲው ኤልያስ ገብሩ የሃገራችን የአሁኑ ሁኔታዋ የእኛ የአስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ሐገራችን ከራሳችን ራስ አትወርድም፡፡ እስራኤላውያን ሐገራቸውን ከምድረበዳነት የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻነት የቀየሩት በአስተሳሰባቸው ነው፡፡ ዛሬ እስራኤል ካለመኖር ወደመኖር መጥታ በሮቦት ቴክኖሎጂ፣ በደህንነት፣ በሕክምና ሳይንስ ረቅቃለች፣ መንጥቃለች፡፡ ይሄ ሁሉ ዕድገት እውን የሆነው በዜጎቿ ጭንቅላት ነው፡፡ ጭንቅላታቸው ከራሳቸው አልፎ ለዓለም ተርፏል፡፡ ልዩነታቸውን አስማምተው በስደት ከሚኖሩበት ሐገር ተሰባስበው ሐገራቸውን እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም. እንደአዲስ ሠርተዋታል፡፡

የእኛ የአብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን ጭንቅላት ግን አዲስ ነገር መፍጠርን ትቶ የተሠራውን ሐገር ለማፍረስ ይቸኩላል፡፡ መናድ እንጂ መካብ የሚያስችል ዕውቀት አላከበትንም፡፡ እርስበርስ ለመጠላለፍ እንጂ ለመተቃቀፍ ስሜታችን እሺ አይለንም፡፡ ‹‹ለልማት የማይሆን ጭንቅላት ለጥፋት ወደር የለውም›› እንዲሉ አባቶቻችን እርስበርስ በክፋት ተለያይተናል፡፡ በጥሎ ማለፍ ፖለቲካ ጠፍተናል፡፡ በሴራ ፖለቲካ ሠውነታችንን ጥለናል፡፡ ይሄን የተዋሃደና የተዋለደ፤ አንድ የሆነ ሕዝብን በወደቀ በብሔር አስተሳሰብ ልንገነጣጥለው ጫፍ ደርሠናል፡፡ ለአምላካችንም አልታመንን፤ ለሐገራችንም አልታመንን፤ ለራሳችንም አልታመንን! የማንነት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ ምን ይሻለን ይሆን??? ሠውነታችን ከርፍቷል!

ወደድንም ጠላንም የአሁኑ የትውልድ አባላት የሃሳብ አብዮት ማስነሳት አለብን፡፡ ብዙ ዘመን በመጠላለፍ፣ በመገዳደል፣ በሴራና በተንኮል እርስበራሳችን ተጠፋፍተናል፡፡ ‹‹ያልሞከርነው ነገር መልካም መሆን ብቻ ነው›› እንዲል ደራሲው አለማየሁ ዋሴ፤ እርስበርስ በፍቅር ገመድ መተሳሰር አለብን፡፡ እርግጥ ነው ፍቅር ራሱ እውቀት ይፈልጋል፡፡ ለማፍቀርም ለመፈቀርም እውቀት ያሻል፡፡ መስራት ያለብን ጭንቅላታችን ላይ ነው፡፡ ገና ያልሞከርነው በጎና ምርጥ ሃሳብ ብዙ አለና እሱ ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ የጎሳ ፖለቲካን አሽቀንጥረን መጣል አለብን፡፡ እንደሠው ሠው ሆነን መኖር መጀመር አለብን፡፡ ሠውነት ከብሔርተኝነት እንደሚቀድም (Humanity before ethnicity) ሠው ሆነን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሕብር፣ ውበት፣ ጥበብ መሆኑን ለዓለም ማሳየት አለብን፡፡ ደጋጎቹና ጠቢባኑ አባቶቻችን ሊቃውንት ይህቺን ሐገር ያቆዩልን በሃይማኖታቸውና በብልሃታቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ እያላት ያነሠች ሆናለች፡፡ ታላቅ ጥበብ በጉያዋ አጭቃ ደንቁራለች፡፡ ሠፊ ሆና ሳለ እኛ ዜጎቿ በመንደር ፖለቲካ አጥብበናታል፡፡ የዛሬ አብዛኛው ፖለቲከኞቻችን አወቅን ሲሉ የደነቆሩ፤ ተጠበብን ሲሉ የጠበቡ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ አዕምሯችን እንደአዲስ ማስጀመር አለብን፡፡ በሕሊናችን ውስጥ የተሰገሰገውን ዘረኝነት አጥፍተን የአንድነትንና የኢትዮጵያዊነትን መረጃዎች መጫን ይኖርብናል፡፡ አልያ በዚህ አያያዛችን አደጋ ላይ ነው ያለነው፡፡ የሚሻለውንና የሚበልጠውን ኢትዮጵያውነት እውን እናድርግ የዛሬው መልዕክት ነው!

ዘረኝነትን አውድመን አዕምሯችንን እንደገና እናስጀምር! (Format racism and Restart our mind)!

እስቲ ሃሳቡን በስንኝ እናጠቃልለው!

ሐገሬ ታማለች! (እ.ብ.ይ.)

ሐገሬ ታማለች፤ ጤንነት የላትም፣ መድሐኒቷን ምሠን፤ እናምጣ ከየትም፡፡

ታውቋል በሽታዋ የ’ራስ ነው ሕመሟ፣ ያሠመማትም ልጇ፤ ፈዋሽዋም ሃኪሟ፡፡

በሽታዋም እኛ! መድሐኒቷም እኛ! የፍቅር ክኒን ነው፤ የህመሙ መዳኛ፡፡

ጤንነት ጎድሏታል፤ ኢትዮጵያ ታማለች፣ በሚድን በሽታ አልጋ ላይ ውላለች፡፡

We have to have an internal idealistic revolution. A revolution starts from our mind and finish to our mind too..! Our problem is the lack of knowledge, lack of love and shortage of positivists. We should format racism and restart our mind!

ቸር ጊዜ!


Comments


bottom of page