የመለስ ልቃቂት
- አዳኙ ካሜራ

- Jan 6, 2019
- 3 min read
Updated: Jan 6, 2019
----
ይህ መጽሐፍ ሲወጣ (ጥቅምት/ህዳር 2009) ዱባይ ነበርኩ። በወቅቱ በኮንትሮባንድ መልክ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ እስከ አንድ ሺህ ብር ድረስ ይሸጥ እንደነበረ ከሶሻል ሚዲያው ማንበቤን አስታውሳለሁ። እኔ ግን ይህንን መጽሐፍ የማንበብ ፍላጎት ያደረብኝ በቅርቡ ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ በመጽሐፉ ዙሪያ የጻፈውን አስተያየት ካነበብኩ በኋላ ነው።
---
ትናንት መጽሐፉን ገዛሁት። ሆኖም ዕድል ከኔ ጋር አልነበረችም። ለኔ የደረሰኝ ኮፒ ብዙ የአርትኦት ስራ የሚያስፈልገው ዓይነት ነው። ኤርሚያስ የጻፈውን የመጀመሪያ መጽሐፍ አንብቤ ስለነበረ በዚህኛው ቅጂ ውስጥ የሚታዩት አታካች ግድፈቶች በእሱ የተፈጸሙ አይመስሉኝም። እንደምገምተው ከሆነ ይህኛው ኮፒ ህገ ወጥ አታሚዎች በድብቅ ያተሙት ነው (የተስፋዬና የዶክተር ብርሃኑ መጻሕፍት በድብቅ እንደሚታተሙት ማለት ነው)።
እንደዚያም ሆኖ ግድፈቶቹ ዋናውን ታሪክ ከመረዳት የሚያግዱ አይደሉም። በውጪ የታተመውን ቅጂ ያነበቡትም ሆነ እኔ የመጽሐፉን ይዘት በእኩል ደረጃ መረዳት እንችላለን።
---
የመጀመሪያ 200 ገጾችን በአንድ ሌሊት አንብቤአለሁ። እናም እንዲህ የሚል ግራ የመጋባት ጥያቄ መጥቶብኛል።
"በእርግጥ ይህንን መጽሐፍ የጻፈው በኢሳት የማውቀው ኤርሚያስ ለገሰ ራሱ ነው? ወይንስ ሌላ ሰው ነው በእርሱ ስም የጻፈው?"
እውነቴን ነው። ኤርሚያስ በኢሳት የሚያቀርበው ትንተና አንድም ቀን ጥሞኝ አያውቅም። በእርሱና በመሳይ መኮንን ዝብዘባዎች የተነሳም ኢሳትን ማየት ትቻለሁ። በተለይ ኤርሚያስ የቀድሞው ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆኑ አንፃር ወያኔ ሁለቱ ትልልቅ ህዝቦች (አማራና ኦሮሞ) ተቀራርበው የትግል አንድነት እንዳይመሠርቱ የማድረግ ተልዕኮ ሰጥቶት ያስኮበለለው ይመስለኝ ነበር። በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችም ኢሳትን ከማየት የሸሹበትን ምክንያት ሲገልጹ ጣታቸውን ወደ ኤርሚያስ ይጠቁማሉ።
በመጽሐፉ ያየሁት ኤርሚያስ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ለሁለቱ ብሄሮች በእኩል ደረጃ ከመቆርቆርና ከመቆጨት ውጪ የማራራቅ ነገር አይታይበትም። በቅድሚያ ያስገረመኝ ነጥብ ይህኛው ነው።
----
በጣም የደነቀኝ ነጥብ ደግሞ ወዲህ ነው!
እኛ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት 27 ዓመታት በእርግጥ እዚሁ ሀገር ውስጥ እንኖር ነበር? የዚሁ ሀገር ዜጎች ነበርን? አካልና አዕምሮአችን በትክክል ይሰሩ ነበርን?
ወዮ! ወዮ! ወዮ! አኒበዴ ጎፍታኮ! ሀገር በቁሟ ተበልታለች።
ህወሓት የተባለው አሸባሪ ቡድን በኢኮኖሚ አውታሮቹ በመጠቀም በሀገሪቱ ላይ የፈጸመውን ውንብድና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰምተናል፣ አንብበናል። ነገር ግን የኤርሚያስን መጽሐፍ ያነበበ ሰው እስከ ዛሬ ድረስ የሰማነው ሁሉ አባይን በጭልፋ ያህል እንደሆነ ይረዳል።
ለምሳሌ እኔ በዚህ ፎቶ ላይ ለብሼው የምታዩትን ኮፍያ የገዛሁት ከመርካቶ ነው። ዋጋው ደግሞ 150 ብር ብቻ ነው። የተሰራበት ጨርቅ ሱፍ ነው። ደግሞ አዲስ እንጂ ሳልቫጅ አይደለም። የሱፍ ኮፊያ በ150 ብር! ዱባይ እንኳ በዚህ ዋጋ ላታገኙት ትችላላችሁ። እንዴት ሊሆን ይችላል?
እንዲህ ዓይነት ወጣ ያለ ነገር ሲገጥማችሁ ከጀርባው የህወሓት ኩባኒያ የሆነው ኤፈርት እንዳለ እወቁ! እሱ ነው ቀረጥ ያልተከፈለበት ኮንቴነር ሙሉ ሸቀጥ እየጫነ የሚያስገባው። ቀረጥ ስላልከፈለበት በርካሽ ዋጋ ይቸበችበዋል። አዳሜ ዋጋው ረክሶ ሲያገኘው ይራኮትበታል። ኤፈርት ደግሞ በዚህ አድራጎቱ ሁለት ነገር ያሳካል። አንደኛ ቀረጥ ሳይከፍልበት በዛ አድርጎ ስለሚያስገባ ብዙ ትርፍ ይዝቃል። ሁለተኛ ቀረጥ የሚከፍሉ ነጋዴዎችን ከገበያ ውጪ ያደርጋቸዋል።
ታዲያ ልብስ ብቻ አይምሰላችሁ። ከምትጠጡት ማኪያቶና ከምትበሉት የምግብ ዘይት ጀምሮ በሁሉም ነገር ውስጥ የኤፈርት ረጃጅም እጆች አሉ። እነዚህ ቀላል ምሳሌዎች ናቸው እንግዲህ። ምሳሌው ከበድ እያለ ሲሄድ ሂሳቡም ከበድ እያለ ይሄዳል።
ይህ ኤፈርት የተባለ ነቀርሳ የሀገሪቱን ባንኮች ያራቆተበት ሂደትና በዛ ያሉ ህጋዊ የንግድ ድርጅቶችን የገደለበት መንገድ ሰፋ ብሎ ተተንትኗል። በሀገር ሀብትና በብሄራዊ ማንነታችን ላይ የፈፀመው ውንብድና በደንብ ተብራርቷል። እያንዳንዱ ትንተና በማስረጃ የተደገፈ መሆኑ በግልፅ ያስታውቃል።
----
መጽሐፉን አሁንም እያነበብኩት ነው። እናንተም ብታነቡት መልካም ነው። በዚህ አጋጣሚ ያሳቁኝን ሁለት ነገሮች ልናገር።
አሉላ ሰለሞን የሚባል ሰው ታውቃላችሁ አይደል? "ያ ሰው አሜሪካ የሚኖረው የኢኮኖሚ ወንጀል ለመስራት ነው" የሚል መረጃ በቅድሚያ የሰጡኝ የሻዕቢያ ምንጮቼ ናቸው። ኤርሚያስ ሌላ መረጃ ደግሞናል። አሉላ አሜሪካ የሚኖረው "ወደ ሀገር ቤት ከገባሁ ወያኔ ይገድለኛል" በሚል ለአሜሪካ መንግስት ባቀረበው ማመልከቻ አማካኝነት የፖለቲካ ጥገኝነት ስላገኘ ነው። ነገር ግን አሁንም ድረስ በግልጽ ለወያኔ እየሰራ ነው። በአንድ በኩል "ወያኔ ሊገድለኝ ነው" ካለ በኋላ በሌላኛው ፊት "ወያኔ ነፍሴ ነው" እያለ ነው። ደመወዝ የሚከፍለውም በአሜሪካ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው። በአሜሪካ ቆይታው መደበኛ ስራው ደግሞ ስለላ ነው። ተመልከቱ! ኤምባሲው መንግስትን ለከዳ ሰው ደመወዝ ይከፍላል።
ስለላን ካነሳን ዘንዳ የኤርሚያስ መጽሐፍ ሚደቅሳ ጫላ ከተባለ ሩቅ ተመልካች የደህንነት ሰላይ ጋር ያስተዋውቀናል። ሰውየው ስራውን ይችለዋል ማለት ብቻ አይገልፀውም። በቃ! ለስለላ የተፈጠረ ነው ለማለት ይቻላል። ከሁሉም የሚገርመው ሚደቅሳ ጫላ ባለፉት ሶስት ዓመታት የታየው ህዝባዊ አመጽ መነሳቱ የማይቀር መሆኑን የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ለመተንበይ መቻሉ። ሚደቅሳ ጫላ በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ እንዳለው "ጉዱ ካሳ" ነው። የህወሓት አመራሮች የገነቡትን ወታደራዊ ጡንቻ በመተማመን "የሚነቀንቀን ኃይል የለም" ብለው በሚያስቡበት ወቅት እርሱ "በህዝቡ ልብ ውስጥ የሚቀጣጠለው የአመፅ እሳት በደንብ ሲጋጋል ፍምና ረመጥ ሆኖ ያጠፋቸዋል" ለማለት የቻለ የሩቅ ተመልካች ነው።
ይህ ሰው የደህንነት አባል በመሆኑ ኤርሚያስ በማንነቱ ዙሪያ ሰፊ መረጃ አልሰጠንም። ነገር ግን የአዲስ አበባ ልጅ መሆኑንና እውነተኛ ስሙ "ማይክ" እንደሚባል ብቻ ነግሮናል። ይህ ሰው ማን ነው? የኦሮሞ ስም እንደ ኮድ የተጠቀመው ለምንድነው? ኤርሚያስ ስለማን እያወራን ነው? ተስፋዬ ኡርጌ ማለቱ ነው? እሱ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን። ከብዙ ምንጮች ለማረጋገጥ እንደቻልኩት ተስፋዬ ኡርጌ የሚደቅሳ ጫላን ያህል አሻግሮ የማየት አቅም ያለው ሰው አይደለም። ስለዚህ ኤርሚያስ ያወራን ያለው ስለሌላ ሰው መሆን አለበት። ---- ይህንን መጽሐፍ አንብቡት! በተለይም አክቲቪስቶች በጣም ይጠቅማችኋል።
![የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ወሎን ወይንም የጥንቱን ቤተ አማራ በሚመለከት የሚያስተጋቡት የፈጠራ ትርክታቸው ሲፈተሽ! [ክፍል ፩]](https://static.wixstatic.com/media/4e50d2_d90ccc98827f4c0ea08a5b7043ac0fe6~mv2.jpg/v1/fill/w_720,h_720,al_c,q_85,enc_avif,quality_auto/4e50d2_d90ccc98827f4c0ea08a5b7043ac0fe6~mv2.jpg)


Comments