top of page

አምስቱ የኢትዮጲያ ሙዚቃ ቅኝቶች

  • Writer: አዳኙ ካሜራ
    አዳኙ ካሜራ
  • Jan 6, 2019
  • 2 min read

Updated: Jan 6, 2019

--------

Collectivism ላይ የመሰረተው የአኗኗር ዘዬአችን በጥበብ ስራችንም ውስጥ ተጋብቶ የጥበብ ባለሞያዎችን ግላዊነት (individuality) ስለሚጋፋው በተጋጋሚ ማህበረሰቡ ጥበብን በራሱ ፍቺ የሚሰጥበት መንገድ ግራ የተጋባ ነው፣ ወይ ተደበላልቋል፡፡ በአደጉት ሃገራት ከፍተኛውን መገለጥ የተቆናጠጡት ትራንስደንታሎቹ እነ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን፣ ቶር፣ ዋልት ዊትማን በጥበብ ስራ ግላዊነትን በእጅጉ አንጸባርቀዋል፡፡ ግላዊነታቸው ስለ ሰብና ሰብዓዊነት ከማሰብ አላሰነፋቸውም ምናልባትም ዊት ማን እንደሚለው በእጅጉ ሰው መሆንን ሰርክ እያከበሩት (celebrate)ካልሆነ በቀር፡፡ ለዛም ይመስላል የሰዎች ባርነት ጭቆና ይሰብረው የነበረው ነጩ ኤመርሰን "we must get rid of slavery or we must get rid of freedom" ያለው፡፡ እነዚህ ፈላስፎችና ባለቅኔዎች በዚህ ግላዊ አቋማቸው ማህበረሰብ ሃሰባቸውን ሳይጠመዝዝባቸው ተመስጦና ማሰላሰላቸው የገለጠላቸውን ለማህበረሰባቸው ሲያበረክቱ ማህበረሰቡም ተቀብሎአቸው ዘመን ተሻግረዋል፡፡

በጥበብ ውስጥ ያለ ግለኝነት ባለሞያው የመሰለውን እና የሃሳቡ ጥግ የደረሰበትን እንዲያደርግ እንዲያበረክት የመፍቀድ ብልሃት ነው፡፡ በርካታውን ጊዜ ይህን ነፃነት የሚነፍግ ማህበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ባለተሰጥኦዎች ከስመው ይቀራሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ራሱን እንዲሆን እድል የተሰጠው ከያኒ የዘመን ክስተት ሊሆን ይችላል፡፡

ዘመን ከእልፍ ጊዜ አንዴ ከሚከስታቸው የጥበብ ባለሞያዎች አንዱ ጎሳዬ ተስፋዬ ነው፡፡ በተለይም ኢንደስትሪው ተቀዛቅዞ የታይታ ስራዎችና እውቅናን ለመሻት በሚሰሩ ተደጋጋሚና አሰልቺ ፈይዳ ቢስ ሃሳቦች በተለየ ለሁለት አስርት አመታት ቀለሙን እና ዘውጉን ይዞ የሰነበተው ይህ ድምፃዊ ለዚህኛው ዘመን፣ የኋላውን ዘመን ስራዎች ባለመደገማቸው ለሚቆጭ የዘርፉ አድናቂ ስጦታ ጭምር ነው፡፡ በኔ እምነት አዲሱ ሲያምሽ ያመኛል አልበም ላይ ጎሳዬ ያጋጠሙት ከላይ ከጠቀስኳቸው ጋር የሚዛመዱ ማህበረሰባዊ ትችቶች ሳይሰብሩት ከነ ጥንካሬው ራሱን ሆኖ መጥቷል፡፡

ከአስራአንድ አመታት በኋላ በአዲሱ አልበም የተከሰተው ጎሳዬን ሰማን- አጀብ ነው! በስራው አዳዲስ እየወጡ ያሉ ድምጻውያንን በማጣመር ከዚህ በፊት እንደለመድነው የሚወደዱ ስራዎች እያስደመጠን ነው፡፡ በእርግጥም የሃገራችን ድምጻውያን መጣመርን ምርጫቸው አያደርጉትም ምክኒያቱ ደግሞ በሃሳቦች መለያየት አለመግባባትን ይጠቅሳሉ፡፡ አመለ ሸጋነቱን ደጋግመን ሲመሰከርለት የሰማነው ጎሳዬ በተለያዩ ጊዜያት መጣመርን እንደ ባህል አድርጎ አሳይቶናል፡፡

አራቱን ቅኝቶች ከፍ ባለ ውበት መጫወት እንደሚችል አንጋፋዎቹ ምስክር ናቸው፡፡ ከቅኝት ወደ ቅኝት ሽግግሩም አስደማሚና ብቃት የሚጠይቅ ለመሆኑ በተደጋጋሚ የሙዚቃ ባለሞያዎች ሲመሰክሩ ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ በመጨረሻው አልበሙ ላይ የታይምስ ጋዜጠኛ መድረክ ላይ አስተውሎት የጻፈውን አንብባችሁ ይሆናል፡፡ ሸጋ ልጅ፣ ላሊበላ፣ ወይን ያስተፈስ፣ አደራ ወዘተ የተሰኙትን ዜማዎች ከላይ በተጠቀሱት ቅኝቶች ውስጥ ሆኖ ሲቻወትም ሰምታችሁት ይሆናል፡፡

በአዲሱ ስራው ግን አንድ የገባኝ ነገር አለ፡፡ ጎሳዬ ተስፋዬ ለሃገራችን ሙዚቃ አምስተኛ ቅኝት ነው!

ተፈጥሮ በእጅጉ አድልታ ለብቻው የቸረችው የሱ ብቻ ቀለም አለ፡፡ ያ ቀለም ከ ባቲ ከአምባሰል፣ ከአንችሆዬና ትዝታ በላይ ነው፡፡ ያ ቀለም ጎሳዬ ብቻ ሲያዜም የሚፈልቅ ነው፡፡ ጋሽ ፀጋዬ ገ/መድህን ከስነግጥም ቀለምና ምጣኔ ድንጋጌዎች በላይ አልፎ በራሱ በመምጣቱ ነበር የፀጋዬ ቤት የሚባል የግጥም አይነት የተዋወቅነው፡፡ እንደዛ ሁሉ ጎሳዬ ብቻ የሚነካካቸው የድምፅ ጥጎች፣ከሱ ብቻ የሚፈልቁ ቀለማት ስላሉም ነው ከቅኝቶቹ በላይ መሆኑን የማምነው፡፡ አልበሙ ሽፋን ላይ የተሰሩ ግድፈቶች ለሌሎችም ለራሱም መማሪያ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ፡፡ የተሻለና ጥንቁቅ ማኔጀር ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ያልኩበትን ምክኒያት ለመረዳት ደግሞ የወዳጁን ቴዎድሮስ ካሳሁንን ስራዎች እንዴት በጥንቃቄ ማኔጅ እንደሚደረጉና የህዝብ ግንኙነት ስራው እንዴት effectively እንደሚሰራ ማየት መልካም ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ፈገግ ያደረገኝን አጋጣሚ ላንሳ፡፡ አንድ ወዳጄን ስለ ፊደል ግድፈቱ ሳነሳበት በስጨት ብሎ “ሙዚቃውን አታዳምጥም ዝም ብለህ?! የሙዚቃ አልበም እንጂ የፊደል ገበታ አላሳተመ !’’

በተረፈ ስለሰጠን ስራ እናመሰግናለን፡፡ በግሌም መልካም እድል እመኝለታለሁ!








Comments


bottom of page